Sunday, April 24, 2011

From Email: The bankruptcy and demise of Harari government

ጥፋትን አርግዘው የነበሩት የሐረሪ ባለስልጣናት በላይ በላዩ አከታትለው ውድቀትን እየወለዱ ቀጥለዋል

ስለ ሐረሪ ክልል ባለስልጣናት እጅግ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ እያንዳንዱን ባለስልጣን ቀረብ ብሎ ላስተዋለ በጣም ያስደነግጣል፡፡ እዚህ ላይ እንደማስጠንቀቂያ ወይም እንደማሳሰቢያ ለመናገር የሚፈልገው የልብ ድካም ወይም የደም ግፊት ያለበት ለሐገሩ የሚያስብ ቅን ዜጋ የሐረሪን ባለስልጣናት ቀርቦ እንዲያይ አይመከርም፡፡ ምክንያቱም በድንጋጤና በመገረም ወዲያው ሊጎዳ ወይም ሊሞት ይችላል፡፡

ሰዎቹ ቀድሞውንም ጥፋትን አርግዘው እንደነበረ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ ያስወርዱታል ወይም አልሆን ካለ ደግሞ አራርቀው ይወልዱታል የሚል ግምት ነበር፡፡ እነሱ ግን የቤተሰብ ዕቅድን ችላ በማለት መንታ መንታውን እየወለዱ አጠቃላይ ክልሉን በውድቀት አጨናንቀውታል፡፡ ለዚህ አባባል ቀለል ያሉ ማስረጃዎችን ከነመገለጫዎቻቸው ሊጥቀስ፣

የሐረር የውሃ ችግር ያበቃለታል ተብሎ ነበር፣ ………………………………………ችግሩ ግን ቀጥሏል፡፡

ሙስና በሐረሪ ክልል ቦታ አይኖረውም ተብሎ ተነግሯል፣ …………….በዚሁ መሠረት ወህኒ ቤቱ በባለስልጣናት ተጨናንቋል፤ በእርግጥ ለምን ታሰሩ ሳይሆን ያልተፈተሹና ያልተነኩ ብዙዎች እንዳሉ እየታወቀ ይባስ ብሎ አሁንም የስልጣን ወንበር ላይ መቀመጣቸው ምን ይባላል?

የክልሉን ዕድገት ለማፋጠን የተቻለው ሁሉ ይደረጋል፡፡ በየደረጃው ያሉ የመንግስት መ/ቤት ኃላፊዎች ሥራንና ሥራን ብቻ ማዕከል በማድረግ ይንቀሳቀሳሉ የሚል እምነት ነበር፡፡
…………………………..ነገር ግን እየሆነ ያለው ተቃራኒው ነው፡፡ ሁሉም ባለስልጣን ስለሥራ ሳይሆን ማን ምን አወራ? ቀጣዩ ታሳሪ ማን ይሆን? በሚል የመንደር ወሬ ተጠምደዋል፡፡ ዛሬ ማን ቤት ምን ተባለ? እንጂ ቢሮ ውስጥ ምን ተሰራ? ብለው አይጠይቁም፡፡ ሐገር መምራትና አሉባልታ ማውራት ተምታቶባቸዋል፡፡

በአብዛኛው የአገርቱ ክልሎች ተግባራዊ የሆነው BPR (Business Process Re-engineering) በሐረሪ ክልል ላይ ገና በወጉ አልተተገበረም፡፡ በተለይ የሐረሪ ክልል ማዘጋጃ ቤትን አሰራር ላስተዋለ መቼውንም በክልሉ BPR በትክክል ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ አይገመትም፡፡ ክልሉን ያጣበቡ ችግሮች እነዚህ ብቻ አይደሉም ግን ለማሳያ ያህል በቂ ይመስሉኛል፡፡

የሐረር ከተማ በሐገሪቱ ውስጥ ካሉ ከተሞች ደረጃ ከመጀመሪያዎቹ ተርታ እንደነበረች ይታወቃል፡፡ አሁን ግን ከታሪክ በስተቀር በብዙ ነገር ተቀድማለች፡፡ ታሪኳንም ቢሆን ስልጣን ላይ ያሉት ማደብዘዝ ስላልቻሉ ብቻ ነው፡፡ ከሌላ ክልል የሚመጡ እንግዶች በሐረር ሁኔታ በጣም ይገረማሉ፡፡ ምክንያቱም ሐረር እራሷን ማስተዳደር ከጀመረች በመንግስት በኩል ምን የተሰራ ነገር አለ? ብለው ሲጠይቁ የሚያገኙት መልስ አጥጋቢ አይሆንላቸውም፡፡  የዚህ ሁሉ ክስረት ዋነኛ ተጠያቂዎቹ ደግሞ ጠያቂ ያጡት ባለስልጣናት መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም አማራጭ ይዞ የተነሳን ድርጅትም ሆነ ግለሰብ እንደ ሕዝብ ጠላት በመቁጠርና ሰዎች ተቀራርበው እንዳይነጋገሩና እናዳይወያዩ ስነ ልቦናዊ ሽብርን በመፍጠር የውድቀት ልጆቻቸውን አከታትለው እየወለዱ ነው፡፡

አሁን አሁን እውነቱ በደንብ ግልጽ እየወጣ እርስ በእርስ የመፈራራት መንፈስ ሰፍኗል፡፡ እውነቱ እያፈጠጠ መደበቅ ሲያቅታቸው ሰዎችን መደበቅ ጀምረዋል፡፡ የሐረር ባለስልጣናት ልብ ሊሉት የሚገባ አንድ ነገር ደግሞ “አንዲት ሴት እርግዝናዋን የፈለገችውን ያህል ቢትደብቅም ካላስወረደችው በስተቀር በራሱ ጊዜ ቆይቶ ምጥ ሲመጣ መታወቁ አይቀርም፡፡ ከዚያ ደግሞ የተፈጥሮ ሕግና ግዴታ እንደመሆኑ ጥፋትን መውለድ፡፡”

ከማጠቃለያ በፊት የተወሰኑ ጥያቄዎችን ሊጠይቅ፤ ለጥያቄዎቹ መልሶቹ በቅድሚያ ሊታወቅ ቢችልም መልስ ሳይሆን መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡

1.      በአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ክልሉን ከማልማት ይልቅ ለማድማት ሁኔታዎችን እያመቻቸ ያለው ክልል የትኛው ነው?
2.      የጨርቅ መጋረጃውን የብረት በር ቀለም በመቀባት ቤቱን ለመቆለፍ የሚታገለው ክልል ማን ተብሎ ይጠራል?

ጥያቄዎቹ የማላገጥ ቢመስሉም የሐረሪ ባለስልጣናት ሕዝቡ ላይ ከሚያላግጡት ጋር ሲተያዩ የተከበሩ ጥያቄዎች ናቸው ለማለት ይቻላል፡፡ መፍትሔው ግን ከጥያቄው በላይ የተከበረ ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ ለዛሬው ከማብቃቴ በፊት ለማጠቃላያ አንድ ነገር ልበል፣

የሐረሪ ባለስልጣናት ግንባሩ ተፈንክቶ ደሙ ልብሱን እንዳይነካ የሚጠነቀቅ ቀሺም ትውልድ እየፈጠሩ ነው፡፡ ይህም እንደ ኅብረተሰብ ወይም እንደ ሐገር ከስረው በግለሰብ ደረጃ ጥቅምን እየፈለጉ ናቸው ማለት ነው፡፡ በቁጥር አራት እንገናኝ፣ ቸር እንሰንብት፡፡   

No comments: