Monday, June 13, 2011

ለአገሩ ብሔራዊ ስሜት ያለው ዜጋ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ ለሚመጣው ትውልድም ያስባል 

Malasayach Comment:

This is a good editorial from Reporter and a lesson for Hararis how to focus on common interests, believe on hard work and show patriotism and love for own country and people.


ርዕሰ አንቀጽ

ከአየር በአየር አስተሳሰብ እንላቀቅ!

Sunday, 12 June 2011

ኢትዮጵያ ከሦስት ሺሕ ዓመታት የበለጠ ታሪክ ያላትና ጥንታዊነት ካላቸውና ቀደምት ከሚባሉት የዓለም አገሮች አንዷ ናት፡፡

የጥቁር ሕዝብ ኩራትና የሰው ዘርም መገኛ ናት፡፡ በዚህ የረዥም ዓመት ታሪኳም፣ ጠንካራና ኃያል ከሚባሉ አገሮች የምትመደብ ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ ጥንት የነበራትን ሥልጣኔ፣ ብልጽግና፣ ሀብትና ኃያልነቷን ማጣት የጀመረችው በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎችና ሒደቶች ሲሆን፣ ዛሬ በድህነት፣ በረሃብተኝነት፣ በማይምነትና በኋላቀርነት ከሚጠቀሱ አገሮች ተርታ ተሰልፋለች፡፡

ኢትዮጵያ ኃያል በነበረችበት ወቅት የማይታወቁ አገሮች አሁን በሰፊ ልዩነት እየመሩን ይገኛሉ፡፡ አገሪቱ ከእንደዚህ ዓይነት አዘቅት ውስጥ ለመውደቋ በርካታ ምክንያቶች ሊቀመጡ ይችላሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ለአንድ አገር ህልውና የሆነው የሞራል ጥያቄ አንዱ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ የነበሩት የሞራል እሴቶች እየተጣሉ አሁን ያለንበት ደረጃ ልንደርስ ችለናል፡፡ ኢትዮጵያ ቀድሞ የነበራትን ኃያልነት ዳግም ማምጣት ትችላለች፡፡ ለዚህም መንግሥትና ዜጐች ተባብረው ሊሠሩ ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች በተለይም ለአፍሪካ በቅኝ ግዛት ባለመገዛት መመኪያ ብትሆንም፣ አገሪቱ አሁን መድረስ ካለባት ደረጃ ላይ ግን አይደለችም፡፡ እንደ ጋና ያሉና በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገሮች ከኋላችን ተነሥተው ጥለውን ሔደዋል፡፡ በየወቅቱም በጎ በሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ስማቸው ይነሣል፡፡ ኢትዮጵያን በመልካም ስም እንድትነሣ ለማድረግ ሁሉም ዜጋ ቆርጦ መነሣት አለበት፡፡

በግሎባላይዜሽን ምክንያት ዓለም አንድ መንደር በሆነችበት በዚህ ዘመን፣ አገሪቱ በኋላቀር አመለካከት ተጠላልፋ መገኘቷ ያሳፍራል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ላይ ከመሥራት ይልቅ እርስ በእርስ መመቀኛኘት ወደፊት እንዳንራመድ ካደረገን ዋነኛው ነው፡፡ አሥር ሰዎች እያንዳንዳቸው ለብቻቸው ትንንሽ ዳቦ ከሚጋግሩ ያላቸውን ዱቄት አዋጥተው አንድ ትልቅ ዳቦ ቢጋግሩ ለብዙ ሰዎች በተረፉ ነበር፡፡ ሆኖም ግን አንዱ ለአንዱ ዕድገት ጥሩ አመለካከት ባለመኖሩ የተነሣ አገሪቱ እየተቀጣች ትገኛለች፡፡ ጥላቻን የመሳሰሉ መርዛማ አመለካከቶች በሕዝቡ ውስጥ እስካሉ ድረስ ብልጽግናን ማምጣት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ እንደዜጋ ሁላችንም ተቻችለን መኖር ካልቻልን የምንናፍቃትን ኢትዮጵያ ልናይ አንችልም፡፡

የአገሪቱ ዜጎች ስለአገራቸው ባህል፣ እምነት፣ ወግና ሥርዓት ጠንቅቀው አውቀው በማንነታቸው የሚኮሩ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ለዚህም ዜጎች ብሔራዊ ስሜት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ለአገሩ ብሔራዊ ስሜት ያለው ዜጋ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ቀጥሎ ለሚመጣው ትውልድም ያስባል፡፡ በመሆኑም ትውልድ ሊረከበው የሚችል አገር ለመገንባት ከታች ጀምሮ እስከ ላይ ድረስ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል በመተባበር ሊሠራ ይገባል፡፡ ስግብግብ በሆነ አመለካከት ብቻ ተመሥርቶ አገርን መቦጥቦጥ የታሪክ ተወቃሽ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ኅብረተሰቡ መልካም አመለካከትን እንደስንቅ በመያዝ ጉዞውን በድል ሊወጣ ይገባል፡፡

አገሪቱን ከድህነት ለማውጣት ከተፈለገም ቁርጠኛና የሥራ ተነሣሽነት ያለው፣ በዲሲፕሊን የሚመራና ጠንክሮ የመሥራት ባህል ያለው ኅብረተሰብ ማፍራት ይጠበቅብናል፡፡ ቻይና በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚዋ በዓለም ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል፡፡ ቻይና ከቅርብ ዓመታት በፊት የምትታወቀው በረሃብና በድህነቷ ነበር፡፡ ሆኖም ሕዝቡ ይህን አስቀያሚ ታሪኩን ለመቅረፍ ካለው ፍላጐት የተነሣ ጠንክሮ በመሥራቱ ገጽታው ሊለወጥ ችሏል፡፡ በዓለማችን የሚገኙ በርካታ አገሮችም በአንድ ወቅት አሳፋሪ ታሪክ የነበራቸው ቢሆንም፣ ያን ታሪካቸውን ለውጠውት አሳይተውናል፡፡ እኛም እነሱ ያደረጉትን ማድረግ የማንችልበት ምንም ዓይነት ምክንያት የለም፡፡

ምዕራባውያን በዕውቀት ላይ ተመርኩዘው በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር የተመሠረቱ በመሆናቸው የዓለምን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር ችለዋል፡፡ በእስያ የሚገኙ በርካታ አገሮችም የምዕራቡ ዓለም የደረሰበትን ሳይንስና ቴክኖሎጂ በተለያዩ ስልቶች በመቅሰም የየአገሮቻቸውን የቴክኖሎጂ ሽግግር አፋጥነዋል፡፡ የተማረ ትውልድ እውቀት፣ ልምድና ችሎታ የአንድ አገር ዕድገትን እንደሚያፋጥንም እሙን ነው፡፡ በመሆኑም በዕውቀት የተገነባ ትውልድ ልናፈራ ይገባናል፡፡ በተለይም ለአገራቸው ዕድገት፣ ልማትና ለውጥ ምክርና ዕገዛ ሊያደርጉ የሚችሉ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ያሉ ዜጐቻችንንም ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡ አገሪቱ የምታስበውንም ዕድገት ልታሳካ የምትችለው በተማረ የሰው ኃይል፣ በዜጐች ጉልበትና በአገሪቱ ሀብት ነውና፡፡

በአገሪቱ ያሉ የትምህርት ተቋሞቻችንም የሞራል እሴት ያለው ብቁ ዜጋን ማፍራት ይገባቸዋል፡፡ ዕውቀት የሌለው ሕዝብ ብዙ ሊጓዝ ስለማይችል ማይምነትን ፈጽመን መዋጋት አለብን፡፡ አገር ልትታደስ የምትችለው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አመራር ሲኖራት ነው    ፡፡ ማንም ዜጋ ራሱ ብቻ የሚከብርበትንና ሀብት የሚያካብትበትን መንገድ ብቻ በማሰብ አገርን ወደኋላ መጐተት የለበትም፡፡ ከራስ በላይ ነፋስ በሚል ብሂል አገሪቷን መቀራመት ህሊና ራሱ አይቀበለውም፡፡

አሁን ያለችው ኢትዮጵያ በርካታ መሰናክሎችን አልፋ ከአባቶቻችን እንደተቀበልናት ሁሉ እኛም ለልጆቻችን ማስተላለፋችን የማይቀር ሒደት ነው፡፡ የተለያዩ ተግዳሮቶች ያሉባት አገር ለመጪው ትውልድ መተላለፍ የለባትም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የሚያስፈልገው መተሳሰብና ቅን የሆነ አመለካከት ብቻ ነው፡፡ ቅጥ ያጣውን የሙስና መረብ በጣጥሰን በመጣል ቀና ትውልድ ማፍራት አለብን፡፡ ሙስና አገርን አፈራርሶ መበተን የሚችል አቅም ስላለው፣ በጊዜ ሊፈታ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

ይህ ትውልድም በታሪክ መዝገብ ላይ በመልካም እንዲሰፍር ከፈለገ፣ አገሪቷን ወደኋላ ከሚያስቀሩ በርካታ ያረጁ አስተሳሰቦች ተላቅቆ ወደፊት መሔድ አለበት፡፡ ራዕይ የሌለው ሕዝብ መረን እንደሚወጣ ሁሉ፣ ራዕይ አልባ ከመሆን መጠበቅ አለብን፡፡ ስለዚህ ለትውልድ የምትተላለፍ አገር ለመመሥረት ከአየር በአየር አስተሳሰብ እንላቀቅ!!

 

No comments: