የሐረሪ ክልል የመሬት አስተዳደር ሹም ተገደሉ
Sunday, 17 April 2011 07:03
የሐረሪ ክልል የመሬት አስተዳደርና የካሳ ክፍያ ኃላፊ የነበሩት አቶ ሐሺም ኢድሪስ በጥይት ተመትተው አዲስ አበባ ኮርያ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ ከትናንት በስቲያ ሕይወታቸው ማለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ረዳት ሳጅን አባስ መሐመድ ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ሟቹ ባለፈው ሰኞ ሮማዳን ኢድሪስና ስዓዲ እድሪስ በተባሉ ወንድማማቾች ባለሀብቶች በቀረቡላቸው የመሬት ጥያቄ ምክንያት አለመግባባት በመፈጠሩ፣ ይህንን ተከትሎ ባለፈው ማክሰኞ በቤታቸው የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ማምለጥ ችለዋል፡፡
አቶ ሐሺም በወቅቱ ለፖሊስ ሪፖርት ማድረጋቸውንና ፖሊስም ተጠርጣሪዎችን ይዞ በዋስትና መለቀቃቸውን፣ ሚያዝያ 5 ቀን 2003 ዓ.ም. ከቀኑ 11፡30 አካባቢ በሐረር ከተማ ጀጎል መሃል ልዩ ስሙ ፈረስ መጋላ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ በተጠርጣሪዎቹ በጥይት ተመተው ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በሟቹ ግድያ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር የዋሉት እነዚህ ግለሰቦች ቀደም ሲል የግድያ ሙከራ አድርገውባቸው በዋስትና የተለቀቁ ሲሆኑ፣ ግድያውን የፈጸሙት እነሱ መሆናቸውንም ፖሊስ ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ሟቹ አዲስ አበባ ኮርያ ሆስፒታል ቢመጡም በተደረገላቸው የሕክምና ዕርዳታ ሕይወታቸውን ማትረፍ ሳይቻል ቀርቶ ባለፈው ዓርብ ከሰዓት በኋላ አርፈዋል፡፡
ገዳዮቹ አላግባብ መሬት ለመውሰድ ያደረጉት ሙከራ በሟቹ እምቢተኝነት ሳይሳካላቸው ቀርቶ ግድያውን መፈጸማቸው ማረጋገጡ የሚገልጸው የክልሉ ፖሊስ፣ በአሁኑ ወቅትም ተጨማሪ ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑንም አስረድቷል፡፡
በየማነ ናግሽ
No comments:
Post a Comment